Home ዜና የአካባቢው ባለስልጣናትም ስለ ዋጋ ጭማሬው መረጃ እየሰጡን አይደለም። … በመንግስት እየቀረበ ያለውን የአፈር ማዳበሪያ ደግሞ አርሶ አደሩ እንዳይገዛ  ታጣቂዎቹ እየከለከሉ ነው ” – አርሶ አደሮች

የአካባቢው ባለስልጣናትም ስለ ዋጋ ጭማሬው መረጃ እየሰጡን አይደለም። … በመንግስት እየቀረበ ያለውን የአፈር ማዳበሪያ ደግሞ አርሶ አደሩ እንዳይገዛ  ታጣቂዎቹ እየከለከሉ ነው ” – አርሶ አደሮች

by admin

በአማራ ክልል መንግስት በሚያስተዳድራቸው አካባቢዎች ያሉ አርሶ አደሮች የማዳበሪያ ዋጋ በእጥፍ መጨመሩ እንዳሳሰባቸው ሲገልፁ ከመንግስት ቁጥጥር ውጪ ባሉ አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች ደግሞ መንግስት ያስወደደውን ማዳበሪያ እስኪቀንስ እንዳይገዙ በታጣቂዎች መከልከላቸውን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

አርሶአደሮቹ ፥ ” የአካባቢው ባለስልጣናት ስለ ዋጋ ጭማሬው መረጃ እየሰጡን አይደለም ፤ በዋጋ ጭማሬው ዙሪያ እና ለሌሎች ጥያቄዎቻችን ማብራሪያ የሚሰጠን አካል አላገኘንም ” ሲሉ ቅሬታቸውን ያቀርባሉ።

በሁለት ሳምንት በአፈር ማዳበሪያ ዙሪያ ለምክር ቤት እንደራሴዎች ቀርበው ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር ) መንግስት በአንድ ኩንታል ማዳበሪያ 3 ሺህ 700 ብር ድጎማ አያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ያነጋገራቸው አርሶአደሮች በዝርዝር ምን አሉ ?

በደቡብ ጎንደር ዞን ሊቦከምክም ወረዳ ነዋሪ መሆናቸውን የሚናገሩት አርሶ አደር አይጠገብ መንግስቱ በዘንድሮው ዓመት የአፈር ማዳበሪያ በመንግስት በስፋት መቅረቡን ይናገራሉ።

ይህ አሰራር ደግሞ ከዚህ ቀደም በጥቁር ገበያ በኩል በውድ ዋጋ አርሶ አደር የሚደርስበትን እንግልትና ምዝበራ ያስቆመ ነው ብለዋል። አርሶ አደሩ አክለውም በመንግስት እየቀረበ ያለው ማዳበሪያ ግን በእጅጉ መወደዱን ይናገራሉ።

ከዚህ ቀድም ኩንታሉን 4 ሺ ብር ይገዙት የነበረው የአፈር ማዳበሪያ ዘንድሮ ግን 8 ሺህ 3 መቶ ብር ሁኗል ብለዋል።

አርሶ አደሩ በአካባቢው ያሉ የመንግስት ባለስልጣናትን የዋጋ ጭማሪውን በተመለከተ ምክንያቱን እንዲነግሩን ስንጠይቅ መልስ አይሰጡንም ሲሉ ገልጸዋል።

ለአርሶ አደሩ ቅሬታ ምላሽ እንዲሰጡን የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አበጀ ስንሻውን የእጅ ስልካቸው ላይ ደጋግመን ብንደውልም ስልኩ ባለመነሳቱ ምላሽ ማግኘት አልቻልንም።

በሰሜን ጎጃም ዞን ባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ ይነሳ ሶስቱ በተባለ ቀበሌ ነዋሪ መሆናቸውን የገለፁልናና ስማቸውን በዘገባው እንዳንጠቅስ የጠየቁን ግለሰብ እርሳቸው የሚኖሩበት አካባቢ በታጣቂዎች በቁጥጥር ስር መሆኑን ገልፀው በመንግስት እየቀረበ ያለውን የአፈር ማዳበሪያ አርሶ አደሩ እንዳይገዛ  ታጣቂዎቹ እየከለከሉ ነው ብለዋል።

ምክንያታቸው ደግሞ ” መንግስት ዋጋውን ያስወደደው አውቆ ነው የሚገዛው ሲያጣ  ዋጋ ይቀንሳል በማለት ነው ” ሲሉ ገልጸዋል።

እኝሁ ግለሰብ አክለውም የታጣቂዎችን ማስጠንቀቂያ ችላ ብሎ ማዳብሪያ የገዛን አርሶ አደር በገንዘብ እየተቀጣ እንደሆነ ተናግረዋል።

” የታጣቂዎችን ማስጠንቀቂያ ያለፈ የማዳበሪያውን ዋጋ 8000 ብር አስከፍለዋል ” ብለዋል።

ከሁለት ሳምንት በፊት በአፈር ማዳበሪያ ዙሪያ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ማብራሪያ የሰጡት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር ) የማዳበሪያ ዋጋ አምራቹ ተምኖ ለገበያ በማቅረቡ ዋጋ መጨመሩን ገልፀው መንግስት ለአርሶ አደሩ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲደርሰው ድጎማ ያደርጋል ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ መንግስት በአንድ ኩንታል ማዳበሪያ 3 ሺህ 700 ብር ድጎማ አያደረገ መሆኑንና በዚህ ዓመትም 84 ቢልየን ብር መንግስት መደጎሙን በዚሁ ወቅት ገልጸው ነበር።

የግብርና ሚንስቴር በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ 24 ሚሊየን ኩንታል ገደማ የአፈር ማዳበሪያ እንደሚያስፈልግ ገልፆ ከዚህ ውስጥ ለ13.4 ሚልየን ኩንታሉ ግዥ መፈፀሙን እስካሁንም ከ4ሚልየን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ  ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱን ከሳምንታት በፊት መግለፁ ይታወሳል።

አጋራ

ተዛማጅ ልጥፎች

Leave a Comment

አንደበት

ለተጠቃሚዎች የቅርብ ጊዜ አካባቢያዊ እና ዓለም አቀፍ ዜና  በማቅረብ ለአንባቢዎች የተሟላ መድረክ የሚሰጥ ዜና ጣቢያ ለአንባቢ ምቹ በይነገጽ እና ሰፋ ያለ የዜና ምድቦች አማካኝነት እንደ ፖለቲካ, ቴክኖሎጂ, መዝናኛ, ስፖርት እና ሌሎችም ባሉ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ወቅታዊ ዜናዎችን ያቀርባል፡፡

ጋዜጣ

አዳዲስ ዜናዎች በቅድሚያ እንዲደርሶት ኢሜሎን በማስገባት ይመዝገቡ

የቅርብ ጊዜ ዜናዎች

@2025 – All Right Reserved.  Powered by Ewenet Communication