በአሁኑ ወቅት በትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ብቸኛ የተቃዋሚው የባይቶና ፓለቲካ ፓርቲ የካቢኔ አባል የሆኑት አቶ ታደለ መንግስቱ በፓሊስ ቁጥጥር ስር ውለው በእስር ወደ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ መደረጋቸው አነጋጋሪ ሆኖ ውሏል።
የካቢኔ አባሉ አቶ ታደለ የመቐለ ማእከላይ ፍርድ ቤት የሚመሩት የመንግስት መስሪያ ቤት እንዲያስፈፅም የሰጠውን ውሳኔ ባለመተግበራቸው ምክንያት ዛሬ ረቡዕ ለ6 ወራት በእስር እንዲቆዩ ቢወሰነባቸውም ከ1 ቀን እስር በኋላ ተለቀዋል።
በምን ምክንያት ታሰሩ ? እንዴትስ ተለቀቁ ?
ተከሳሹ የትግራይ የትራንስፓርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ታደለ መንግስቱ ሲሆኑ ከሳሽ ደግሞ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ነው።
የክሱ ፍሬ ነገር በትግራዩ ጦርነት የተወሰደችበት ላንድ ክሩዘር V8 መኪና እንድትመለስለት የሚጠይቅ ነው።
ባለስልጣኑ ዓይነቷና የሰሌዳ ቁጥሯን ጠቅሶ በቢሮው አስፈፃሚነት እንድትመለስለት የጠየቀባት ላንድ ክሩዘር V8 መኪና የህወሓት ፅህፈት ሃላፊዋ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/ሄር ሲጠቀሙባት ነበር።
የጊዚያዊ አስተዳደሩ የትራንስፓርት ቢሮ V8 መኪናዋ ለባለቤቱ እንድትመለስ እንዲያስፈፅም የቀረበበት ክስ በመቀበል የህወሓት ፓርቲ ሃላፊዋ (ወ/ሮ ፈትለወርቅ) እንዲመለሱ ተጠይቀው አሻፈረኝ በማለታቸው ምክንያት ፍርድ ቤት ጉዳዩን ማስፈፀም ያልቻሉትን የቢሮውን ሃላፊ (አቶ ታደለ) በእስር እንዲቀርቡ ያዛል።
ዛሬ ሚያዝያ 15/2017 ዓ.ም በፓሊስ ተይዘው ፍርድ ቤት የቀረቡት ሃላፊው ጉዳዩ እንዲያስፈፅሙ በተደጋጋሚ የቀረበላቸው ባለመተግበራቸው ምክንያት ለ6 ወር እንዲታሰሩ ይፈርዳል።
ሂደቱ እንዲህ እያለ ወደ ባለቤትዋ እንድትመለስ ጥያቄ የቀረበባት V8 መኪና ሚያዝያ 15/2017 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ በሸኚ ደብዳቤ በኤግዚብትነት ወደ ፓሊስ እጅ በመግባቷ ምክንያት ሃላፊው ከእስር ሊለቀቁ ችለዋል።
ከትግራይ የትራንስፓርት ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በጦርነቱ ምክንያት ከመንግስታዊና ግለሰቦች ተወስደው በማይመለከታቸው አካላት የነበሩት ከ 2800 በላይ ተሽከርካሪዎች ወደ ባለቤቶቹ ተመልሰዋል።