በኢትዮጵያ የሮቦቲክስ ሻምፒዮና ውድድር የተጀመረው በቅርቡ ቢሆንም፣ በውድድሩ ከሀገር ውስጥ አልፎ በአኅጉር አቀፍ ደረጃ በአጭር ጊዜ አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ተወዳዳሪዎች በተወዳደሩበት ሜዳ በማሸነፍ የሀገራቸውን ስም ማስጠራትም ጀምረዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት በተካሄዱ የአፍሪካ ሮቦቲክስ ሻምፒዮና ውድድሮችም ይሄው ታይቷል፡፡
የአፍሪካ የሮቦቲክስ ሻምፒዮና ውድድር በየዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን፣ ሰሞኑን የተካሄደው ውድድርም ለሶሰተኛ ጊዜ የተዘጋጀ ነው፡፡ ኢትዮ ሮቦ ሮቦቲክስ የተሰኘው ድርጅት ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ይህ የአፍሪካ ሮቦቲክስ ሻምፒዮና የ2025 ውድድር ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በሳይንስ ሙዚየም ተካሂዷል።
በዚህ የአፍሪካ የሮቦቲክስ ሻምፒዮና ውድድር የመንግሥት፣ የግልና በኢትዮጵያ የሚገኙ የዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡ ውድድሩ የዲዛይን፣ የምህንድስና፣ የፕሮግራም አወጣጥ እና የቡድን ሥራ ችሎታን ለማስፋትና በዘርፉ ያለውን አቅም ለማጎልበት ያለመ መሆኑ በመድረኩ ተጠቁሟል፡፡
በሮቦቲክስ ውድድሩ ተሳታፊ ከሆኑት ተማሪዎች መካከል ተማሪ ሄራኒ አብነትና ጓደኞቿ ይገኙበታል፡፡ እነ ተማሪ ሄራኒ የብሪቲሽ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት ተማሪዎች ናቸው፡፡ ተማሪ ሄራኒ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን፣ ጓደኞቿ ከዘጠነኛ እስከ አስራ አንደኛ ባሉት የክፍል ደረጃዎች የሚማሩ ናቸው፡፡ ተማሪዎቹ ሮቦት ሰርተው ለውድድሩ ቀርበዋል፡፡
ተማሪዎቹ በትምህርት ቤታቸው በኩል የመጣውን ይህን የውድድር እድል ለመጠቀም በቅድሚያ በኢትዮ ሮቦ ሮቦቲክስ የተዘጋጀ ስልጠና ተሳትፈዋል፡፡ ስልጠናው በትምህርት ቤት ከሚማሩት ትምህርት ባሻገር ስለሮቦቲክስ አዲስ እውቀት እንዲያገኙና ብዙ እውቀት እንዲጨብጡ እንዳስቻላቸው ተማሪ ሄራኒ ገልጻለች፡፡
ሮቦቲክስ በወደፊቱ ሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ሚና አለው ስትል ተናግራ፣ ለዚህ ዝግጁ መሆን የሚያስችል ስልጠና ማግኘታቸውን ተናግራለች፡፡ ከዚህ ባሻገር ስለሮቦቲክስ በጥልቀት ለማወቅና ለመማር በእጅጉ እንደሚያስፈልግም አስታውቃለች፡፡
ስልጠናው በሮቦቲክስ ዘርፍ ፍላጎቱና ተሰጥኦ ላላቸው ተማሪዎች መሰጠቱን ጠቅሳ፤ ስልጠናውን ከወሰዱ በኋላም በትምህርት ቤቱ ከዘጠነኛ እስከ አስራ አንደኛ ክፍል ድረስ ያሉ 23 ተማሪዎች በበድን ሆነው ሮቦቱን መስራታቸውን ትገልጻለች፡፡ የጨዋታ ሮቦት በደንብ ሠርተው በውድድሩ አሸናፊ ለመሆን መጋጀታቸውን ጠቅሳ፣ ሀገራቸውን በሮቦቲክስ ዘርፍ ማስጠራት እንደሚፈልጉም ተናግራለች፡፡
በልጅነት እድሜ ውስጥ እንደመሆናችን መስራት የሚጠበቅብን የጨዋታ ሮቦት ነው ያለችው ተማሪዋ፣ ስለሮቦቲክስ እየተማርን የጨዋታ ሮቦት በመስራት ለማሸነፍ መፎካከር አንዱ ሥራ ነው ብላለች፡፡ ከዚያም ደረጃችንን እያሳደግን ሌሎች ለሀገር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ሮቦቶችን መስራት እንችላለን ›› ትላለች፡፡
ተማሪዎች በሮቦቲክስ ለመስልጠንም ሆነ ለመሳተፍ ሰዓት የለንም ብለው ሊያሰቡ ቢችሉም ውስጡ ገብተው ሲያወቁትና ሲማሩት በጣም የሚወዱት ብዙ ነገሮችን ሊሰሩበትና ሊፈጥሩበት የሚያስችላቸው ምቹ ሁኔታ የሚያመላክታቸው ነው ያለችው ተማሪዋ፤ ከብዙ ተማሪዎች ጋር እንዲቀራረቡ በቡድን መስራት እንዲለምዱ እንደሚያስችል ትገልጻለች፡፡
‹‹ሮቦቲክስ አስተሳሰባችንን ይቀይራል፤ በጥልቅ በማሰብና ማሰላሰል ምን አይነት ሮቦት መስራት እንደምንችል በደንብ እንድናውቅ ይረዳናል›› ስትል ገልጻ፣ ቴክኖሎጂ ይበልጥ እየዘመነ ከመሄዱ ጋር ተያይዞ የሮቦቲክስ ቴክኖሎጂ በእጅጉ አስፈላጊና አይቀሬ ነው፤ በዚህ ላይ ከአሁኑ መለማመድና በቂ እውቀት መያዝም ያስፈልጋል ›› ትላለች፡፡
ሌሎቹ የውድድሩ ተሳታፊዎች ተማሪ ኢንትሳር ኑርና ጓደኞቿ ደግሞ ከመካኒሳ አባድር ትምህርት ቤት ነው ለውድድሩ የቀረቡት፡፡ እነ ተማሪ ኢንትሳር የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ሲሆኑ፣ ለአንድ ዓመት ያህል በኢትዮ ሮቦ ሮቦቲክስ ስለሮቦቲክስ ስልጠና ወስደው ሮቦት ሰርተውም ነው ለውድድሩ የቀረቡት፡፡
ተማሪ ኢንትሳር፤ በሮቦቲክስ መሰልጠን የሚፈልጉና ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎች ከትምህርት ቤቱ ተመርጠው ስልጠናውን እንዲወስዱ መደረጉን ትገልጻለች፡፡ እሷ እንዳለችው፤ ወደ ሮቦቲክስ ስልጠናው ከገቡ በኋላ ታዳጊዎች እንደመሆናቸው እድሜያቸውን የሚመጥን ስልጠና አግኝተዋል፡፡ በሮቦቲክስ ዙሪያ ሊኖራቸው የሚገባ መሰረታዊ እውቀት በስልጠናው አግኝተዋል፡፡ ስልጠናውን በሚገባ ከወሰዱም በኋላ በቡድን ሆነው፣ በእያንዳንዱ ቡድን አስር ተማሪዎች ተደልድለው፣ እየተረዳዱ ሮቦቶችን ሰርተው ለውድድር አቅርበዋል፡፡
ስልጠናውን የወሰዱ ሁሉም ተማሪዎች ችሎታቸው እና አቅማቸው እየታየ ሮቦቱን መስራት ላይ እንዲሳተፉ መደረጉን ጠቅሳ፤ የተወሰኑት ተማሪዎች በኮዲንጉ፣ የተወሰኑት ደግ በሮቦቲክሱ እውቀት፣ የተቀሩት ደግሞ ሮቦቱን በማንቀሳቀስ ሥራ ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ ሁሉም ተማሪዎች የተሳተፉበት ሮቦት መስራቱን አስታውቃለች፡፡
ሮቦታቸው ‹‹ራፒድ ሪሌ›› የሚባል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፣ ፈጥኖ ኳስ ሰብስቦ በበቂ ሁኔታ ኢላማ የተደረገበት ቦታ ላይ ማስገባት የሚያስችል የጨዋታ ሮቦት መሆኑን አብራርታለች፡፡ ይህንን ለመፈጸም በጣም ጥቂት ደቂቃዎች ብቻ እንደሚወስድበትና በጣም ፈጣን ሮቦት መሆኑን ትናገራለች፡፡ ሮቦቱን በደንብ እንደ ሰሩትና በውድድሩ አሸናፊ እንደሚያደርጋቸውም አመላክታለች፡፡
እነ ተማሪ ኢንትሳር፤ በዚህ በአፍሪካ ሮቦቲክስ ውድድሩ ካሸነፉ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው የሮቦቲክስ ውድድር የመሳተፍ እድሉ አላቸው፡፡ ‹‹ሮቦቲክስን የተማርነው የራሳችንን ክህሎት ለማሻሻል ብቻ ሳይሆን አገራችንን በሮቦቲክሱ ዓለም ላይ ለማስተዋወቅ ነው›› ስትል ተማሪ ኢንትሳር ጠቅሳ፣ ወደፊትም በዚህ ዘርፍ በደንብ ሰርተው ራሳቸውንና ሀገራቸውን ለማስተዋወቅ ዓላማ እንዳላቸው ጠቁማለች፡፡
የተሰጠን ስልጠና ሮቦቲክስን በደንብ እንድናውቅ ረድቶናል፡፡ ይህን እድል ላመቻቹልን አካላት ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ የምትለው ተማሪዋ፤ በተለይ በሰው ስራሽ አስተውሎት ላይ መስራት ለሚፈልጉ ታዳጊዎች ሮቦቲክስ መነሻ መሰረት እንደሚሆናቸውም ጠቁማለች፡፡ ይህን በደንብ እንዲያወቁትና እንዲሰሩበት ማድረግ ያስፈልጋል ብላለች። ይህ ስልጠና ከመሠረቱ ጀምሮ የሮቦቲክስ ግንዛቤያቸው በደንብ ማሳደግ የሚችለቡት መሆኑንም ጠቅሳ፣ ይበልጥ በትኩረት ሊሰራበት ይገባል ባይም ናት፡፡
በመድረኩ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ጊዜ ዓለም የሰው ልጅ ከደረሰበት የእድገት ደረጃ አኳያ ስትታይ የቴክኖሎጂ እድገት፣ የፈጠራ ፍጥነትና ጥራት የአገራት ተወዳዳሪነትና ተፎካካሪነት እንደመለኪያ መስፈርት በሚወሰዱበት ከፍተኛ ውድድር ውስጥ ትገኛለች ፡፡ በዚህ ዘመን የሰው ሠራሽ አስተውሎት፣ ሮቦቲክስና የመሳሳሉት አስፈላጊ ብቻ ሳይሆኑ የሕልውና ጉዳይ እየሆኑ መጥተዋል ብለዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚ ልማትን ለማረጋገጥ በከፍተኛ ትጋት እየሰራች ትገኛለች፡፡ ለቴክኖሎጂ ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ ተደራሽ፣ አካታች፣ ፍትሕታዊነቱና ደህንነቱ የተረገገጠ እንዲሆንና ቀጣይነት ያለው የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባትም እየተሰራ ይገኛል፡፡
በተለይም ዘርፉን በፖሊሲ፣ በስትራቴጂ፣ በፕሮግራሞች በማገዝና በመደገፍ ለዘርፉ ምቹ የሆነ ምህዳር እንዲኖር ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ጠቅሰዋል። ከዚህ በፊት ተሰጥኦ፣ ፍላጎትና ክህሎት ያላቸው ወጣቶች ሥነ ምህዳሩ ምቹ ባለመሆኑ የተነሳ አመቺ ነባራዊ ሁኔታ ወደአለበት አካባቢ ይሰደዱ እንደነበርም አስታውሰዋል።
በሀገር ውስጥ የተፈጠረውን ምቹ ምህዳር በፖሊሲ በመደገፍ ተሰጥኦ፣ ፍላጎትና ክህሎት ያላቸው ዜጎች በዘርፉ እንዲሰሩ፣ በዘርፉ ልምድና ክህሎት ያላቸው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ወደ ሀገራቸው መጥተው እንዲሰሩ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ለዘርፉ የሚያስፈልግ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለመሳብ የሚያስችል የምህዳር ግንባታ ስራም እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡