ማታ ማታ ባል ያምረኛል !
ከአበባ ብርሃኑ
አበባ ይዞ ከስራ የሚመለስ፣ ሲገባ ደግሞ ብሔሬን እስክረሳ ድረስ የሚስመኝ ፣ አንገቴን ስሞ ትንፋሼን የሚያዳምጥ፣ የልብ ምቴን አስተካክሎ ሲጨርስ አዋዋሌን የሚጠይቀኝ ፣ ራት ሳቀራርብ የሚያግዘኝ ፣ የመጀመሪያውን ጉርሻ ለኔ የሚያጎርሰኝ፣ አንዴ ጎርሶ ሙያየን የሚያደንቅልኝ ፣ ከራት በሁዋላ ዋይን ቀድቶ የሚያቀብለኝ፣ አጠገቤ ሆኖ እየዳበሰ ውሎውን የሚተርክልኝ — የሚያማክረኝ ምናምን —-
ይህን ሁሉ ፍለጋ ፍቅር የሚያውቅ ሰው አገባሁ ።
ባገባሁት በነጋታው ፍቅረኛ መሆኑ ቀርቶ አባዎራ ሆነ ።
ውሎ ሲያድር ማታ ማታ
‘የት ነህ?’ እያልኩ ሶስት ጊዜ መደወል ጀመርኩ፣ ስልኩ ስለማይነሳ
‘ደንበኛችን ከአገልግሎት መስጫ ክልል ውጪ ናቸው– ‘ ከምትለው ሴት ጋር ዝምድና ፈጠርን ። -‘ደህና ነሽ ?’ ‘አስቸገርኩሽ እንግዲህ ‘ ምናምን እላት ጀመር።
እሷም ተጨንቃ
‘ ምን ታረጊዋለሽ አብዛኛው ባሎች እንዲህ ናቸው ‘ ብላኝ ታውቃለች።
አመሻሽቶ ሲገባ የአበባ ሽታ ሳይሆን ቢራ ቢራ እያለ መግባት ጀመረ በእጁም ኮቱን አንጠልጥሎ ስለሚገባ በእጅም ሳንነካካ እንቀራለን።
ሲገባ አያየኝም ፣ ሻሽ ልሰር ወይ አናቴ ላይ ድመታችንን ልሸከም አያይም ።
እራት ሳቀርብ ቲቪ ይከፍታል :—
ሳቀርብ ሳያየኝ ይጎርሳል ‘ ባለሙያ’ በሚል ሙገሳ ፋንታ ‘እስኪ ወጥ ነገሩን ጨምሪበት ‘ ይለኛል።
በልቶ ሲነሳ ማፅዳት እቀጥላለሁ እሱ ቲቪ ማየት ይቀጥላል ፣ ኳስ ከፍቶ ይመሰጣል ‘ዋው ‘ እያለ ግብ ያደንቃል። አንዲት ድብልብል ጉድ ከኔ መብለጥዋ ያናድደኛል —
ቢቸግረኝ የባልን አትኩሮት መሳቢያ ስድስት ሺህ መንገዶች የሚለውን መፅሃፍ ገዝቼ አንብቤ
ራሴን አሳምሬ ፣ ስስ ፒጃማ ለብሼ: እንዲያየኝ ፊት ለፊቱ መወዝወዝ ጀመርኩ። አትኩሮት ለመሳብ ነበር — እሱ እቴ
‘እስኪ ቲቪውን አትከልይኝ ‘ ብሎኝ ቁጭ።
አትኩሮት ለመሳብ የማደርገው ሁሉ አተካሮ ያስነሳብን ጀመር።
ልንተኛ ስንል ትራሱን ያቅፋል ፣ ስነካው ያንኮራፋል ፣ ያ ነገር ላይማ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀበት ይመስላል
— አለ አይደል ወዲያው ተሳፍሮ ቅርብ ይወርዳል ፣
በቃ:- አልጠራሁም እንጂ ወያላ በሉኝ :-
በር ከፍቶ ማስገባት እና ማውረድ ነገር።
ሁለት ሜትር አልጋችን ምንም ካልተጠቀምንበት የቤት ዕቃችን መሃል አንዱ ሆነ።
አብረን ከወጣን አለባበሴን የሚያደንቀው ሰውየ አሁን እራቁን ልውጣ ልልበስ ፣ ቦርሳ ልያዝ የቤታችንን ቡችላ ልዘል አያይም።
ወር ሲደርስ እንደ ኦዲተር አብረን ወጪ እና ገቢ መደመር ሆነ ስራችን ።
ሲመስለኝ ባለቤቴ ድሮ ሳንጋባ የነበረውን ፍቅሩን ሰርጋችን ላይ ‘ሎጋሽቦ ‘ ሲጨፍር እና ሲዘልል ሳይጥለው አይቀርምና ሲወድቅበት ያየ ወይም የወደቀበትን የሚያውቅ ቢያሳውቀኝ ወሮታ ከፋይ ነኝ።