ከዚህ በኋላ 4 ኪሎ ቤተመንግስት ዙሪያ ያሉ መንገዶች በአንድ አቅጣጫ ብቻ አገልግሎት እንደሚሰጡ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ አስታውቋል።
በመሆኑም ፦
- ከጥይት ቤት እስከ ፓርላማ ትራፊክ መብራት፣
- ከቤተመንግስት ፖርክንግ እስከ ጥይት ቤት
- ከፓርላማ ትራፊክ መብራት እስከ ሳይንስ ሙዝየም ድረስ ያሉ መንገዶች ቀድሞ ከነበረው ባለሁለት አቅጣጫ መንገድ ወደ አንድ አቅጣጫ መንገድ ተቀይረዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ክበበው ሚደቅሳን መስመሮቹ እንደ ቀድሞው ባለ ሁለት አቅጣጫ ሆነው አገልግሎት መስጠታቸውን መቼ ይጀምራሉ ? ሲል ጠይቋል።
በምላሻቸው በአንድ አቅጣጫ እንጂ ወደበፊቱ ተመልሶ በሁለት አቅጣጫ አገልግሎት እንደማይሰጡ ገልጸዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ አስቀድመው ” ለሁለት ቀን ወደ አንድ አቅጣጫ (One way) ተደርገው አገልግሎት ይሰጣሉ ” በሚል ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸው ነበር።
ሆኖም ” ለሁለት ቀን ያልኩት በአንድ አቅጣጫ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ የሚሰሩ ስራዎች እና የጎደሉትን የማሟላት ስራ ለመስራት ነው ” ሲሉ መንገዶቹ በቀጣይነትም ባለ አንድ አቅጣጫ መንገድ ሆነው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።
አክለውም ” የትራፊክ ስራ ዳይናሚክ ነው፣ እንደ የአስፈላጊነቱ በየጊዜው የማሻሻል ስራዎች ሊኖሩ ይችላሉ ” በማለት ጠቁመዋል።
ከዚህ በኃላ ግን መንገዶቹ ባለ አንድ አቅጣጫ ብቻ እንደሆኑ አስገንዝበዋል።