አሜሪካ ወደ 30 የሚጠጉ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ዲፕሎማቲክ ጽሕፈት ቤቶቿን ልትዘጋ መሆኑን ሮይተርስ የአገሪቱን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሰነድን ጠቅሶ ዘገበ።
የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር አብዛኞቹ በአፍሪካ እና በአውሮፓ የሚገኙ ቢያንስ 27 የአሜሪካ ኤምባሲዎች እና ቆንስላዎችን የሚዘጋ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ጎረቤት ሀገር #ኤርትራ አንዷ ናት።
በውሳኔው መሠረት ይዘጋሉ የተባሉት አስሩ የአሜሪካ ኤምባሲዎች ፦
- በኤርትራ፣
- በግሪናዳ፣
- በሌሶቶ፣
- በማዕካላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣
- በሉክዘንበርግ፣
- በሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ፣
- በጋምቢያ፣
- በደቡብ ሱዳን፣
- በማልታ እና በማልዲቭስ የሚገኙ መሆናቸውን ሮይተርስ የተመለከተው ሰነድ ያመለክታል።
ከሚዘጉት ኤምባሲዎች እና ቆንስላዎች ባሻገር ኤምባሲ እና በርካታ ቆንስላዎችን በመያዝ ግዙፍ የዲፕሎማቲክ ሥራ በሚከናወንባቸው እንዳ ጃፓን እና ካናዳ ያሉትን ተልዕኮዎች በማዋሃድ መጠናቸውን የመቀነስም ሐሳብ አለ።
ሰነዱ ከፍተኛ ወጪ በማስወጣት ውድ የዲፕሎማሲ ተልዕኮ የተመደበባቸው ናቸው ያላቸውን በሞቃዲሾ ሶማሊያ እና በኢራቅ ያሉ የዲፕሎማቲክ አባላትን መጠን የመቀነስ ሐሳብም መቅረቡን አመልክቷል።
ዶናልድ ትራምፕ ወደ ፕሬዝዳንትነት ከተመለሱ በኋላ የአሜሪካ መንግሥት በተለያዩ መስኮች ከአገሪቱ ፍላጎት ጋር አይጣጣሙም ያላቸውን ተቋማት በመዝጋት እና እርዳታዎችን በማቋረጥ ላይ ይገኛል።
የትራምፕ የቅርብ ሰው በመሆኑት ማርኮ ሩቢዮ የሚመራው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በጀት እስከ ግማሽ የሚደርሰውን እንደሚቀነስ ሮይተርስ የተመለከተውን የመሥሪያ ቤቱን ሰነድ ጠቅሶ አመልክቷል።
በዚህም ሳቢያ በበርካታ አገራት የሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲዎች እና ቆንስላዎችን የመዝጋት ሐሳብ ሀሳብ ነው ያለው።
የአሜሪካ መንግሥት ለውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ከሚያወጣው ገንዘብ ወደ 30 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ለመቀነስ አቅዶ የበጀት ጥያቄውን ለአገሪቱ ምክር ቤት ለማቅረብ እየተዘጋጀ ነው።
መረጃው የሮይተርስ እና ቢቢሲ ነው።