በትግራይ መምህራን ማህበር ጠበቆች የቀረበውና በጦርነቱ ጊዜ ያልተከፈለ የ17 ወራት የመምህራን ደመወዝ ሲመለከት የቆየው ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ዛሬ ሚያዝያ 7/2017 ዓ.ም ባዋለው ችሎት ውሳኔውን ሰጥቷል።
ተከሳሾቹ የትግራይ ትምህርት ቢሮ ፣ የፋይናንስ ቢሮ ፣ የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር እንዲሁም የገንዘብ/ የፋይናንስ ሚንስቴር ሲሆኑ ጉዳያቸው በሌሉበት ሲታይ ቆይቷል።
ፍርድ ቤቱ የቀረበለት ክስ መርምሮ የመምህራኑ የ17 ወራት ውዙፍ ደመወዝ እንዲከፈል ወስኖ ፋይሉ ወደ መዝገብ ቤት መልሶታል።
የፍርድ ቤቱ ውሳኔ እንደሚቀበሉትና እንዳረካቸው የተናገሩት አስተያየት ሰጪ መምህራን ውሳኔው ቶሎ በመተግበር በከፋ ሁኔታ የሚመገኙ መምህራን መታደግ ይገባል ብለዋል።
ተከሳሾቹ ውሳኔው በማስመልከት እስካሁን ያሉት ነገር የለም።
መምህራን ያካተተ የ17 ወራት ያልተከፈለ የመንግስት ሰራተኞች ውዙፍ ደመወዝ የመከፈል ጥያቄ ከፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ማግስት የጀመረ ነው።
በቀድሞ ፕሬዜዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ጊዚያዊ አስተዳደር ጉዳዩ በፍርድ ቤት እንዳይታይ የሚከልክል መምሪያ እስከማውጣት ደርሶ ነበር።