Home ስፖርት የዋንጫ ከበርቴዉ ስንብት!!

የዋንጫ ከበርቴዉ ስንብት!!

by admin

#Ethiopia | የመግለጫዉ የመጀመሪያው ቀጠሮ እሮብ ነበር፡፡አልተሳካም፡፡ለቀጣዪ ቀን ሀሙስም አልሆነም፡፡ ከ አንተነህ እና ወ/ሮ በየነች ጋር ተነጋግረን ለትላንት አርብ አዘጋጀነው፡፡ ስፖርት ዞን-Sport Zone ከመኳንት እና ከሰዒድ ጋር ስቱድዮ እንደወጣን በፍጥነት ወደ መግለጫው ሄድን፡፡

ዋናው ሀሳብ ለአስራት የተደረገ ድጋፍን ለማመስገን እናም ቀጣዪን ለማስታወስ ነው፡፡ Anteneh Alamerew እና Andargachew Solomon ያሰባሰቡት 1.2ሚልየን ብር በባለቤቱ በየነች አካውንት መድረሱንም ለየሰጪዎች ይፋ ማድረግንም ይመለከታል፡፡

“ትንሽ ተስፋ እያየን ነው፡፡ደም ከወሰደ በኋላ ፊቱ መለስ ብልዋል፡፡በአይኑም ምላሽ እየሰጠን ነው፡፡ፈጣሪ የማይሳነው ነገር የለም፡፡የሱን ተአምር እንጠብቃለን፡፡” ወ/ሮ በየነች ሰለሞን በተስፋ ስሜት ተናገረች፡፡

ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ Abiy Ahmed Ali እና ለከንቲባ አዳነች አበቤም Adanech Abiebie- አዳነች አቤቤ ጥሪ አቀረበች፡፡

“ስለ 2029 አፍሪካ ዋንጫ ሲነገር አስራት ለእግር ኳሱ እዚህ መድረስ ካደረገው ነገር አንጻር እንደሚያስታውሱት ተስፋ አለኝ፡፡ለአለማየሁ እሸቴ እና ለሌሎች በየዘርፋ ታሪክ ለሰሩ ሰዎች ዶክተር አብይ ጉብኝት እና ድጋፍ አድርገዋል፡፡አስራትንም አይረሱትም ብዬ አስባለሁ፡፡ውድድሩ ሲደረግ አስራት ነቅቶ በቦታው እንደሚገኝም አምናለሁ”ወይዘሮ በየነች ሰለሞን በብሩህ ስሜት ተናገረች፡፡

አንተነህም አስራትን አመሰገነ፡

” እዚህ ላይ የደረስኩት በሱ ነው፡፡ አስራት የተቆጣኝ የሰደበኝ እና የመከረኝ የዛሬ ማንነቴን ሰጥቶኛል፡፡”

ይህ መግለጫ የሚሰጠው በአስራት መኖሪያ ቤት ነው፡፡እሱ ከተኛበት ክፍል አጠገብ!

በማሽን እርዳታ እየተነፈሰ ለአንድ አመት ከ3ወር አስራት የአልጋ ቁራኛ ሆንዋል፡፡

መግለጫው ተጠናቆ አስራት ያለበትን ሁኔታ ለመመልከት በቃን፡፡ለመግለጽ በሚከብድ ሁኔታ ገጽታው ተቀይርዋል፡፡አጠገቡ ለመተንፈስ የሚረዳ መሳሪያም አለ፡፡ከእኔና Mequanenet Berhie Haile በተለየ አንተነህ በአስራት ሁኔታ ተስፋ አድርግዋል፡፡

“አሁን እንደውም ለውጥ አለው፡፡ለመጨረሻ ጊዜ ሳየው አልቅሼ ነበር የወጣሁት” አለን፡፡

ይህንን ተስፋ በልባችን ይዘን ነበር የወጣነው፡፡ዜናው እና ጥሪው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶር አብይ ይደርሳል የሚል ተስፋም ነበረን፡፡በየነች የእግር ኳስ ወዳዱ የድሬ ከንቲባንም ከድር ጁሀርንም @Keder Juhar ተስፋ አድርጋ ነበር፡፡ቤተሰቡ በድሬ ብዙ ታሪክ አለውና፡፡ለይድነቃቸው ቦቼ ያደረጉትንም በማስታወስ…

አንዳርጋቸው ሰለሞን ምሽት ላይ የfacebook live እያሰናዳ ነበር፡፡የርእሱንም ጉዳይ አውርተን ፎቶዎቹን ላኩለት፡፡ ምሽት2 ሰአት ላይ Alula Frew በNBC Tv የቀኑን ዜና እያስተላለፈ ነዉ፡፡እኔም ቁጭ ብዬ እያየሁ…

ድንገት ግን ያ ሁላ የቀኑ ተስፋ መብነኑን የኑራ ስልክ አሳወቀኝ፡፡

አላህ ነገሮችንየሚያገጣጥመው በራሱ መንገድ ነው፡፡እኛ እናስባለን እሱ ያለው ይፈፀማል፡፡ለካ አስራትን ለመጨረሻ ጊዜ እንድናየው ነበር መግለጫውን ያዘገየው…የዋንጫው ከበርቴ ጉምቱው ሰው አለፈ፡፡
……………………………………………………………………

አስራት ሀይሌ በኢትዮጲያ እግር ኳስ የወደር የለሽ ስኬታማነት ተምሳሌት ነው፡፡በተጫዋችነት የ10ኛው አፍሪካ ዋንጫ አባል ነበር፡፡የተከላካይ ክፍሉ መሪ ሆኖም ተጫውትዋል፡፡ኢትዮጵያ ላይ የተሰናዳው የመጨረሻው አፍሪካ ዋንጫ መሆኑ ነው፡፡የ2029ኙ ከተሳካ ከነ አስራት 53 አመታት በኌላ ይሆናል፡፡

በክለብ አስራት የቅዱስ ጊዮርጊስ ምልክት ነው፡፡በክፋ ቀን የደረሰ ጀግናም ጭምር!!

በክለብ ደረጃ በዳርማር፣ ድሬደዋ ጥጥ ማህበር እና ትግል ፍሬ ባለ ታሪክ ነው።

አስራት ጫማ ሰቅሎ ማሰልጠን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በዋንጫ ያሸበረቀ የአሰልጣኝነት ህይወት ነበረው፡፡ትልቁ ታሪኩ በቅዱስ ጊዮርጊስ ነው፡፡
👌1976 በቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመሪያ ድሉ ወደ አንደኛ ዲቪዝዮን ከፍ ያደረገበት ዋንጫ ነው::1977 የኢትዮጲያ ሻምፕዮን እያለ 24 ዋንጫዋችን አሳክትዋል፡፡

አጋራ

ተዛማጅ ልጥፎች

Leave a Comment

አንደበት

ለተጠቃሚዎች የቅርብ ጊዜ አካባቢያዊ እና ዓለም አቀፍ ዜና  በማቅረብ ለአንባቢዎች የተሟላ መድረክ የሚሰጥ ዜና ጣቢያ ለአንባቢ ምቹ በይነገጽ እና ሰፋ ያለ የዜና ምድቦች አማካኝነት እንደ ፖለቲካ, ቴክኖሎጂ, መዝናኛ, ስፖርት እና ሌሎችም ባሉ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ወቅታዊ ዜናዎችን ያቀርባል፡፡

ጋዜጣ

አዳዲስ ዜናዎች በቅድሚያ እንዲደርሶት ኢሜሎን በማስገባት ይመዝገቡ

የቅርብ ጊዜ ዜናዎች

@2025 – All Right Reserved.  Powered by Ewenet Communication